የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች
1. ራዕይ
አገራዊ ራዕይ
በሕዝብ ተሳትፎና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማሕበራዊ ፍትህ የነገሰባት ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ፡፡
የክፍለ-ኢኮኖሚው ራዕይ
አምራች፣ ለመኖሪያ ምቹና ዘመናዊ ከተሞች እንዲሁም ተወዳዳሪ የሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና ደረጃውን የጠበቀና የተመጣጠነ የመንገድ አውታር ተስፋፍቶ ማየት፡፡
የተቋሙ ራዕይ
የዕድገት ማዕከል የሆኑ፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባቸው ከተሞች እና ብቃት የተላበሰ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ አውታር ተስፋፍቶ ማየት የሚያስችል ብቃት ያለው ሞዴል ተቋም ሆኖ መገኘት፡፡
2. ተልዕኮ
የክፍለ-ኢኮኖሚው ተልዕኮ
የኢትዮጵያ ከተሞች ቀልጣፋና ውጤታማ ህዝባዊ አገልግሎት ለነዋሪው ህብረተሰብ እንዲያቀርቡ፣ የገጠር ልማቱን እንዲደግፉና እንዲያፋጥኑ የሚያስችሉ የአሰራር ስልቶች በመቀየስ፣ የተሳትፏዊ ዲሞክራሲ ተምሳሌት እንዲሆኑ የሚያስችሉ የመልካም አስተዳደር ፕሮግራሞችን በመንደፍና ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም ለከተማ ነዋሪው በተለይም ለወጣቱ የስራ እድል ሊፈጥሩና ገቢውን ሊያሻሽሉ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን ለማከናውን የሚረዳ አቅም በከተሞች መገንባት፤
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በቀጣይነት አቅሙን በማጎልበት አገራዊውን ፍላጎት በማርካት በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆንና በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የግንባታ ፍላጎት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ የሚያስችል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ፕሮግራምን ተፈፃሚ ማድረግ፤
የመንገድ አውታር ሁሉንም የሃገሪቱ ክፍሎች የማስተሳሰር ተልዕኮውን ለማሳካት እንዲችል፣ የመንገድ ግንባታ ማከናወንና ለነባር መንገዶች ጥገና እና ለአዲስ ግንባታዎች አስፈላጊውን ፋይናንስ ከማግኛ ምንጮች በበቂ ሁኔታ ማሰባሰብ፤
የተቋሙ ተልዕኮ
በአገራዊ ራእይ ላይ ተመርኩዞ የተነደፈውን የሚኒስቴር መ/ቤቱን ራዕይ ለማሳካት የማስተባበሪያ ቢሮዎችንና ተጠሪ ጽ/ቤቶችን በመምራትና ልዩ ልዩ መንግሥታዊና የግል ሴክተር፣ የማህበረሰብና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻና አጋዥ ተቋማትን በማስተባበርና በማቀናጀት እንዲሁም የተጠናከረና ቀጣይነት የተላበሰ የአቅም ግንባታ ኘሮግራም በመንደፍ በከተሞች መልካም አስተዳደር የሚሰፍንበትን፣ የተሳለጠና ውጤታማ ከተማ ነክ አገልግሎት የሚቀርብበትን፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉም የግንባታና የአገልግሎት አሰጣጥ አቅም የሚጎለብበትና የመንገድ ልማትና እንክብካቤን ለዘላቂነት ማብቃት ነው፡፡
3. እሴቶች
ሚኒስቴሩ ዓላማውን ለማሳካትና የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት የሚከተሉትን እሴቶች አንግቦ ተነስቷል፡፡
3.1 ስትራቴጂክ እሴቶች
- ለለውጥ መስራት - ለውሱን ሀብት ውጤታማ አጠቃቀም ትኩረት መስጠት
3.2 ኦፕሬሽናል እሴቶች
- ምንጊዜም ለተገልጋይ የተሟላ እርካታ ቅድሚያ መስጠት - ምቹ የሥራ አካባቢና መልካም የሥራ ግንኙነትን መፍጠር - ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት - አቅምን አሟጦ መጠቀም፣ - የፆታ እኩልነት መርሆአችን ነው
3.3 የሠራተኞች የግል እሴቶች
- የተቋሙ ተልዕኮ የእኔም ተልዕኮ ነው - ለሚሰጠኝ ተቋማዊ ኃላፊነት ተጠያቂ ነኝ - ምንጊዜም ለተሻለ አፈፃፀም እቆማለሁ - ለአዳዲስ ሃሳቦችና አሰራሮች ዝግጁ ሠራተኛ፣
|